Skip to main content

በክልሉ በመገንባት ላይ የሚገኙ የመጠጥ ውሃ ፣ የመስኖና የመንገድ ልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ ።

ታህሳስ 21/2018 (ወልቂጤ)

በክልሉ በመገንባት ላይ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ስራዎች አፈፃፀም አስመልክቶ ከመሰረተ ልማት ክላስተር የተወጣጡ አመራር አካላትና የሚመለከታቸው በተገኙበት ድጋፋዊ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ።

በድጋፋዊ ክትትሉ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሙላቱ ጡሞሮ እንደገለፁት በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የመጠጥ ውሃ ፣ የመስኖ ተቋማት እና የመንገድ ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።

በዛሬው ዕለት የመስክ ምልከታ ከተካሄደባቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች መካከል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ጉብሬ ዲስክሪት እየተሰራ የሚገኘው የወልቂጤ ቃጥባሬ 23 ኪ.ሜ ጠጠር መንገገድ፣  በሪካፕ ፕሮግራም በእኖር ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የወርቃት ሻፎም አጨወደ 11.7 ኪ.ሚ አዲስ የጠጠር መንገድ ስራ እና ቸሀ ወረዳና እኖር ወረዳን የሚያገናኘው ባለ 28 ሜትር ደረጃውን የጠበቀ የዊንቀ ድልድይ ግንባታ አፈፃፀም ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ በሚያስችል አሰራሮች ላይ ከሚመለከታቸው የስራ ተቋራጮች ጋር መነጋገራቸውን አቶ ሙላቱ ገልፀዋል ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ወሰን ባሻህ በበኩላቸው በመሰረተ ልማት ክላስተር የሚገኙ ተቋሟት በተቀናጀ መንገድ ድጋፋዊ ክትትል በመደረጉ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ባጣረ ጊዜ እንዲቀረፍ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር በሴክተሮቹ እና ባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ያጠናክራል ብለዋል ።

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ አበራ አርፊጦ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥራት ተገንብተው በወቅቱ ተጠናቀው ለማህበረሰቡ ተገቢውን አግልግሎት መስጠት እንዲችሉ በክልሉ መንግስት እና በክላስተር ደረጃ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረው በመስክ ምልከታው በታዪ ነጥቦች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል ።

በተያያዘም በተደረገው ድጋፋዊ ክትትል የታዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች አፈፃፀማቸው አበረታች ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የክልሉ መስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አማካሪ አቶ ደግፌ በቀለ ተናግረዋል ።

በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ጉብሬ ዲስክሪት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ በርታ እና የዳምኮን ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ገብሬ የጠጠር መንገዶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ተገቢው የሰው ኃይል እና የስራ መሳሪያዎች በማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ በድጋፋዊ ክትትል ለተሰማሩ አካላት ገልፀው በነዳጅ አቅርቦትና በሌሎችም እየተደረጉ የሚገኙ ድጋፎች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል ።

በመስክ ምልከታው ከክልሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት አመራሮች በተጨማሪ ከጉራጌ ዞን ፣ ከአበሽጌ፣ ከቸሃ እና ከእኖር ወረዳዎች የተወጣጡ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል ።

ድጋፋዊ ክትትሉ በቀጣይ ቀናት በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ።

Image