ቢሮ ኃላፊ መልእክት
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ መልእክት
አቶ ዳዊት ሃይሉ ጌሮ
ኢትዮጵያ አገራችን በተለያዩ ወንዞች፣ ጅረቶች፣ ሐይቆች እና የውሀ አካላት የታደለች እና በተፈጥሮ ፀጋ የተቸረች ሀገር ከመሆኗም በላይ በአስራ ሁለት ትላልቅ የውሀ ተፋሰሶች የተከፈለች አገር ናት፡፡ ምንም እንኳን የተለያዩ ወንዞችና ሐይቆች ባለቤት ብንሆንም የውሀ ሀብቶቻችንን እንደ ሀገር ሙሉ በሙሉ በተገቢው መንገድ መጠቀም አለመቻላችን በውስጣችን ቁጭት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር የውሀ ሀብቶቻችንን እና የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንን በአግባቡ በማልማት፣ በማበልፀግና ለዜጎቻችን ምቹና ተስማሚ በማድረግ ጥቅም ላይ ለማዋል የውሀ ሀብቶቻችንን የማልማት፣ የማስተዳደር፣ የመንከባከብ እና በተገበው መንገድ ለመገልገል በመንግስት ረገድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሰጥ ከላይ ከተገለጹት እንደ አገር ካሉን አስራ ሁለት ተፋሰሶች መካከል ሁለት ትላልቅ የኦሞ ጊቤ እና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች በክልላችን በሚገኙ አካባቢዎች የሚያቋርጡና በርካታ የክልልን ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተፋሰሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ተፋሰሶች በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢከኖሚያዊ ጥቅሞች ለክልሉ ማህበረሰብ የሚሰጡ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው የግልገል ግቢ ሁለት የውሀ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በኦሞ ጊቤ ተፋሰስ ላይ የተመሰረተና በየም ዞን ውስጥ የሚገኝ የተፋሰሱ ትልቁ ቱሩፋትና ልዩ ትኩረት የሚፈልግ አካባቢ ነው፡፡
በተጨማሪም በክልሉ የተለያዩ ወንዞችና ጅረቶች የሚገኙበት ከመሆኑም በላይ አነስተኛ የውሀ ኃይል ምንጭ አገልግሎት የሚሰጡ ለአብነት በሐዲያ ዞን በጊቤ ወረዳ ጊሴዳ አነስተኛ የውሀ ኃይል ምነጭ በቅርቡ ተመርቆ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ እና በሌላ በኩል በአመካ ወረዳ ተጨማሪ አነስተኛ የውሀ ኃይል ምንጭ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑ የውሀ ሀብቶቻችንን እንደ ክልል በአግባቡ ለመጠቀም እየተደረጉ ያሉ ጅምር ጥረቶችን ማሳያና በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በክልሉ በርካታ ወንዞች ከመኖራቸው ባሻገር የተወሰኑ ሐይቆች (ቦዮና ትንሹ አባያ) የሚገኙበት ለመስኖ አገልግሎት የሚውል እንዲሁም ለዓሳ ሀብት ልማት የሚያገለግሉ የውሀ ሀብቶች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡ በሌላ በኩል በክልላችን ለቱሪዝም መዳረሻ የሚያገለግሉ በርካታ ፏፏቴዎች እና ፍል ውሀዎች የሚገኙበት ክልል ነው፡፡
ለውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር የክልላችንን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሀ ችግር መፍታት ዋነኛ ጉዳይ ነው፡፡ ለህዝባችን የንፁህ መጠጥ ውሀ የማቅረብ እና በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ በመሰረታዊነት ውሀ ለሰው ልጆች ጤንነት ወሳኝ የሆነ፣ የኑሮ ደረጃ ሁኔታ የሚያመላክት፣ ምርታማነት የማሳደግ እድምታ ያለው ከመሆኑም በላይ ድህነት የመቀነስ በአጠቃላይ ቀጣይነት ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከማረጋገጥ አንፃር ትልቅ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ጉዳይ ለሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት የማሟላት ጉዳይ በመሆኑ አሁንም በክልላችን የንፁህ መመጥ ውሀ ጥያቄ ያልተመለሰላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በገጠሩና በከተማ የንፁህ መጠጥ ውሀ ሽፋን ከፍ የማድረግ እንዲሁም የማይሰሩና በብልሽት የቆሙ የውሀ ተቋማትን በመጠገን የንፁህ መጠጥ ውሀ ተደራሽነት የማሳደግ ሥራ መሰራት ይኖርበታል፡፡
በሌላ በኩል ክልላችን የገፀና የከርሰ ምድር የውሀ ሀብት እንዲሁም የማዕድን የአለኝታ ጥናት በማካሄድ የተለያዩ የውሀና የተፈጥሮ ፀጋ የሆኑትን ማዕድናት በማፈላለግ በውጤታማናትና በቅልጥፍና ከመጠቀም አንፃር ያጋጠሙ ችግሮችና ማነቆዎች በመፍታት እና ተገቢውን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥና በመከተል የክልሉን እምቅ የውሃና የማዕድን ሀብት በመለየት ሥራ ላይ እንዲውል ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ተቋማችን ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር በውሀ በመስኖ፣ በማዕድናና በአማራጭ ኢነርጂ ክልላችን ለምቶ ህዝባችንን በፍትሀዊነት፣ በቅንጅት እና በዘላቂነት ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
በተጨማሪም በክልላችን የገፀና የከረስ ምድር የውሀ ሀብት ለንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ ለአማራጭ ኢነርጂ ምንጭነት፣ ለመስኖ አውታር ግንባታ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም እና ከዚህም በላይ ለሆኑ ሌሎች አገልግሎቶች ማዋል የሚችል አቅም ያለን መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ እነዚህን አቅሞች በተገቢው መንገድ በማስተዳደር፣ በማልማትና በመጠቀም የክልላችን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም የውሀ ሀብቶቻችንን የክልላችን የልማት አውታር ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል አድርጎ በመጠቀም በኢኮኖሚና በማህበራዊ ረገድ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ትስስር በመፍጠር በተፋሰሱ የሚገኙ ክልልች በጋራ አብሮ የማደግ እና የመልማት እንዲሁም ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ከታች እስከ ላይ በቅንጅት ለጋራ ልማት መትጋትን ይጠይቃል፡፡
በአጠቃላይ የክልሉን የውሀ ሽፋን የማሳደግ፣ የመስኖ ልማት ተደራሽነት የመጨመር፣ የማዕድንና የአማራጭ ኢነርጂ ልማት ሥራችን የማጎልበት እንዲሁም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማሳለጥ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራና ልዕቀት በማሳደግ የውሀና የማዕድን እምቅ አቅም በመጠቀም ረገድ መስሪያ ቤታችን በትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡ በዚህም የተግባር ውጤታማነትና የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መላውን ህዝንና በተለይ የግል ባለሀብቱን በሴክተሩ ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች በማሳተፍ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት በልዩ ትኩረትና ቅንጅት የሚሰራ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ የቅንጅት አድማሶቻችንን ማስፋት የሚያስችሉ አማራጮችን በመጠቀም ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሻገር ብሎም አገራዊ ለውጥና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ርብርብ በምናደርግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የምንገኝ መሆኑን በመረዳት በከፍተኛ መሰጠትና ትጋት ደከመን ሰለቸን ሳንል የምንሰራ መሆኑን አረጋግጣለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!!!
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 
