Skip to main content

የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ግንባታን ለማፋጠን የማቺንግ ፈንድ ክፍያዎችን በወቅቱ ማጠናቀቅ እንደሚገባ የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም (ወልቂጤ)

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በከንባታ ዞን የዱራሜ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ግንባታ አፈፃፀም አስመልክቶ የመስክ ምልከታና ውይይት ተካሂዷል።

በመስክ ምልከታው የተገኙት የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሃላፊ ካሳዬ ተክሌ (ኢ/ር) እንደገለፁት በአንዳንድ ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማፋጠን የማቺንግ ፈንድ ክፍያዎችን በወቅቱ በማጠናቀቅ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የዱራሜ ከተማን የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል በመንግስትና በሚመለከታቸው አካላት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያስታወቁት ኢ/ር ካሳዬ የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ አካላት በጊዜ የለንም ስሜት በፍጥነትና በጥራት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።

በቢሮ ኅላፊ ማዕረግ የቢሮው ምክትል ሃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ በባለቤትነት የመከታተልና የመደገፍ ስራው ሳይቆራሩጥ ሊመራ እንደሚገባ ገልፀው የፕሮጀክቱ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ላይ የታየው መጓተት ሊታረም እንደሚገባ አመላክተዋል።

የቢሮው አማካሪ አቶ ሃይሌ ደዊ በበኩላቸው በመደመር መንግሥት አመራር የሕብረተሰቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀው በመስክ ምልከታው ነጥረው የወጡ መልካም እሴቶችን በማስፋትና ክፍተቶችን በማረም ተገቢው ሊፈፀም ይገባል ብለዋል ።

የከንባታ ዞን ዋና አስተዳደሪ ልዩ አማካሪ አቶ ደነቀ ደልከሶ በበኩላቸው የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት ምልከታ ማድረጉን አድንቀው በተሰጠው ግብረ መልስ መሰረት የፕሮጀክቱን አፈፃፀም ለማሻሻል ተገቢው እንደሚፈፀም ጠቁመው የክልሉ መንግስት፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ቢሮው የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም በፕሮጀክቶቹ ላይ በተካሄደው የመስክ ምልከታ ጎልተው በወጡ ነጥቦችና ዙሪያ ቀሪ ተግባራት በሚፈፀሙበት አግባብ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በምልከታው የቢሮው የስራ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የፕሮጀክቱ አማካሪዎች፣ የተቋራጭ ድርጅት ሚመለከታቸው፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

Image