ለገራድ ቢመዶ አጠቃላይ ሆስፒታል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሟላት የጥናትና ዲዛይን ሥራ መጀመሩ ተገለፀ ።
ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም (ወልቂጤ)
በማረቆ ልዩ ወረዳ በኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ በግንባታ ላይ ለሚገኘው ለገራድ ቢመዶ አጠቃላይ ሆስፒታል ዘላቂና አስተማማኝ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለመፍጠር የመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ሥራ በይፋ ተጀምሯል።
የሥራው መጀመር የሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሳደግና ለታካሚዎች እንዲሁም ለሕክምና ባለሙያዎች አስተማማኝ የውሃ አገልግሎት ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እንዲፋጠን መመሪያ የተሰጠው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር እንዳሻው ጣሰው ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ የመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት የሰርቬይንግ፣ የለቀማና የቴክኒክ መረጃ ማሰባሰብ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
የመጠጥ ውሃ ጥናቱ የውሃ ምንጭን መለየት፣ የውሃ መጠንና ጥራትን መገምገም፣ የቧንቧ መስመሮችን አቅጣጫ መወሰን፣ የውሃ ማከማቻና ስርጭት ስርዓትን መንደፍ እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ተስማሚ የሆነ የቴክኒክ ዲዛይን ለማዘጋጀት መሠረት እንደሚሆን ተገልጿል።
የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ የመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ አብዮ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የሚከናወነው ጥናት የተሟላና የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ የውሃ አቅርቦት ሥርዓት ለመዘርጋት መሠረታዊ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።
የጥናትና ዲዛይን ሥራው በቴክኒክ ደረጃ ተገቢውን ጥራት ጠብቆ እንዲከናወን እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አበራ የሆስፒታሉን የአሁንና የወደፊት የውሃ ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ የተሟላ የቴክኒክ ዲዛይን ለማዘጋጀት ባለሙያዎች በትኩረት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ይህ ሲጠናቀቅ የሆስፒታሉ የሕክምና አገልግሎት በንፁህ ውሃ እጥረት እንዳይስተጓጎል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።
አቶ አበራ በክልሉ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ተቋማት የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማስፋፋት ቢሮው በተቀናጀ ሁኔታ እየሠራ እንደሚገኝና ለገራድ ቢመዶ አጠቃላይ ሆስፒታል የተጀመረው ሥራም የዚሁ እቅድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የማረቆ ልዩ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሰለ ከድር በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉ ሲጠናቀቅ ለልዩ ወረዳው እና ለአካባቢው ሕዝብ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ የንፁህ መጠጥ ውሃ መኖር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆስፒታል ያለ አስተማማኝ የውሃ አቅርቦት የተሟላ አገልግሎት መስጠት አይችልም ያሉት ኃላፊው የታካሚዎች ሕክምና፣ የቀዶ ጥገና አገልግሎቶች፣ የንፅህና ሥርዓቶችና የኢንፌክሽን መከላከል ሁሉም በቂ የንፁህ ውሃ አቅርቦትን ይፈልጋሉ ብለዋል።
ስለዚህ የተጀመረው ጥናት የሆስፒታሉን የወደፊት አገልግሎት ስኬታማ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ሲሉም ኃላፊው ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ የሕንፃ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የውሃ አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ከወዲሁ ጥናትና ዲዛይን መጀመሩ የተገቢ እርምጃ መሆኑን የገለጹት አቶ መሰለ፣ የክልሉ መንግሥትና የውሃ ቢሮ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ሲል የልዩ ወረው መንግስት ኮምንኬሽን ዘግቧል።
See less
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 