Skip to main content

በቸሀ ወረዳ በሸሬና ቆንደሮቻ ቀበሌ ጥልቅ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ሀምሌ 26/2018 ዓ ም

በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ በሸሬና ቆንደሮቻ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ያንቤ ጃቱ በተባለ መንደር ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር የተገነባ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በዛሬው ዕለት በድምቀት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

ይህ ማህበረሰቡን ከውሃ ችግር የታደገ ፕሮጀክት እውን የሆነው በኢትዮጵያ ገነት ቤተክርስቲያን፣ በአንቤ ጃቱና አራራዳ ሼህ ገነት አጥቢያ ቤተክርስቲያን እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ በተደረገ የተቀናጀ የጋራ ርብርብ ነው።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊና የቸሀ ወረዳ ደጋፊ አመራር)፣ የቸሀ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ዋና የመንግስት ተጠሪ እና ሌሎች የወረዳው አመራሮች ተገኝተዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ገነት ቤተክርስቲያን እና የአጥቢያ ቤተክርስቲያኗ አመራሮች እንዲሁም የኤሊም ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ አመራሮች በክብር እንግድነት ታድመዋል።

የጉራጌ ዞን ውሃና ማዕድን መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ እንደተናገሩት የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ጥያቄን ለመመለስ መንግስት ከሚያደርገው ሰፊ ጥረት ጎን ለጎን፣ ቤተክርስቲያኒቱ እና ማህበረሰቡ ያደረጉት ይህ ተግባራዊ ትብብር እጅግ የሚያስመሰግንና ለሌሎችም ትልቅ አርዓያ የሚሆን በጎ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበረሰቡ ይህንን በከፍተኛ ወጪ የተገነባ የውሃ ተቋም በአግባቡ በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና ከብልሽት በመጠበቅ የረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ የባለቤትነት ድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሱ ድንቁ እንደተናገሩት ይህ የውሃ ፕሮጀክት በወረዳው በተለይም በያንቤ ጃቱ መንደር የነበረውን የውሃ እጥረት በዘላቂነት በማቃለል እናቶችን ከእንግልት የሚታደግ ትልቅ የልማት ስራ ነው ብለዋል።

ውሃ የሁሉም ነገር መሰረትና የህይወት ምንጭ ነው የሰው ልጅ ሲወለድ ወደዚች ምድር የሚቀበለው በውሃ ታጥቦ ነው፤ በህይወት ዘመኑ ሁሉ በውሃ ተጠቅሞና ተገልግሎ ሲያልፍም ወደ መጨረሻው ማረፊያው የሚሸኘው በውሃ ታጥቦ ነው ስለዚህ ውሃ የሰው ልጅ የህልውናው አልፋና ኦሜጋ ነው በማለት የውሃን የህይወት መሰረትነት አብራርተዋል።

ወረዳው ይህን መሰል የልማት አጋርነቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥማት ከመፍታቱም ባሻገር ለሌሎች አካባቢዎች የመንግስት፣ የህዝብና የተቋማት የልማት ትብብር ማሳያ ይሆናል ብለዋል

የኢትዮጵያ ገነት ቤተክርስቲያን ዋና ፕሬዝዳንት ፓስተር ታምራት ታሪኩ እንደገለፁት ቤተክርስቲያኒቱ ከነፍስ አድን መንፈሳዊ አገልግሎቷ ባለፈ፣ የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና ስጋዊ ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

ኤሌም ኢንተርናል ኢትዮፕያ ኮንተራቱ ወስደው ሰርተው በዛሬው እለት አስረክበዋል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው ይኸው የውሃ ፕሮጀክት ቤተክርስቲያኗ ለማህበረሰቡ ያላትን አጋርነት በተግባር ያሳየችበት መሆኑን አብራርተዋል።

See less

Image