Skip to main content

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 207 የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ከ600 ሺህ ህዝብ በላይ በንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጉን ቢሮው አስታወቀ ።

ሰኔ 30/2018 ዓ.ም (ወልቂጤ)

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የውሀ ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸም በወልቂጤ ከተማ ለመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች በተዘጋጀው መድረክ ተገምግሟል ።

በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት በመንግስት በአጋር አካላትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በክልሉ በገጠርና በከተማ 207 አዲስና ነባር የውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት 619,382 የህብረተሰብ ክፍሎች በንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ ገለፁ ።

ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተቋረጡና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ የክልሉ መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም በውሀ ዘርፍ ለተመዘገበው ውጤቶች የሠራተኞች ሚና እጅግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው የገለፁት አቶ ዳዊት በአዲሱ በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

በመጠጥ ውሀ ግንባታ እና በጥናትና ዲዛይን ስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ሊቀርፉ የሚችሉ ዘመናዊ የቅየሳ መሣሪያና ቴክኖሎጂ ቢሮው ግዥ በመፈፀሙ ሥራዎች በጥራት የሚሰሩበት እንዲሁም ይባክን የነበረን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ማዳን መቻሉን ከዚህም በላይ የፈፃሚዎችን ውጤታማነት ያሳደገ መሆኑን ገልፀዋል።

በተቋሟት አስተዳደር ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በመልካም አስተዳደር ችግሮች አፈታት ላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አበረታች ተግባራት ቢከናወንም ካለው የሕዝብ ተጠቃሚነትና እርካታ አንፃር ሰራተኛው ለቀጣይ ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል ብለዋል ።

በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የክልሉ ውሀ ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትልና የውሀ ሀብት ጥናትና አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር በጀት ዓመቱ ቢሮው ካስቀመጠው ግብ አኳያ በአጣብቂኝ ችግር ውስጥ ገብተው የነበሩ ፕሮጀክቶች በተቀናጀ መንገድ ችግሮቻቸውን በመፍታት ማጠናቀቅ መቻሉን ገልፀዋል ።

የውሀ ጥራት ቁጥጥር ላይ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ያመላከቱት ወ/ሮ አለይካ በውሀ ተቋማት ቆጠራ፣ የላብራቶሪ አቅም ግንባታና በሎሎች ተግባራት በተመዘገበው ውጤት መዘናጋት ሳይፈጠር ሰራተኛው ለቀጣይ ተግባር ራሱን ዝግጁ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በቅርበት ከመፍታት አኳያ በአመራሩና በባለሙያው መካከል የታየው ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው ከመድረኩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የቢሮውን ተልዕኮ ለማሳካት በሙሉ አቅም እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

See less

Image