በቀቤና ልዩ ወረዳ በ"ሀይራት ያርዲም" ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት በኡጉማ ሄራምባ ቀበሌ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ተገለፀ ።
ወልቂጤ ፣ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ በ"ሀይራት ያርዲም" ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት በኡጉማ ሄራምባ ቀበሌ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ተገልጿል ።
በምረቃው ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ ዳዊት ሀይሉ እንደገለፁት በክልሉ በሁሉም አከባቢ የሚነሱ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።
በተጨማሪም አዳዲስ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ በመንግስት በጀትና ሌሎች አጋር የልማት ድርጅቶችን በማሳተፍ የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሽፋንን ለማሻሻል በከፍተኛ ጥረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በዛሬው እለት በቀቤና ልዩ ወረዳ የተመረቀው ፕሮጀክትም የዚሁ አካል መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም የክልሉ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል ።
በተመሳሳይም የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድአሚን በደዊ እንዳሉት ዛሬ በኡጉማ ሄራምባ ቀበሌ ተገኝተን ያስመረቅነው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የፓርቲያችንን ብልፅግና ዋነኛ መርህ የሆነው "ሰው ተኮር" ልማትን በተግባር የሳየ ነው ብለዋል።
አክለውም እንደ ልዩ ወረዳ የህዝባችንን መሰረታዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በገባነው ቃል መሰረት ሌት ተቀን እየሰራን እንገኛለን ያሉ ሲሆን በቀጣይም በልዩ ወረዳው የሚመረቁ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል ።
በተጨማሪም የፕሮጀክቱ መመረቅ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ለብዙ ዓመታት ይነሳ የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ የሚመልስ መሆኑን ጠቁመው ለአከባቢው ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
በሌላ በኩልም የልዩ ወረዳው ውሃ፣ መአድንና ኢነርጂ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጁሀር ጀማል በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ እና ጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል ።
በተጨማሪም የፕሮጀክቱ መመረቅ የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ካለው ፋይዳ በተጨማሪ፣ በተለይም እናቶችና ህጻናት ውሃ ፍለጋ የሚጓዙበትን ርቀትና ድካም የሚቀንስ በመሆኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀው ተግባሩ እንዲሳካ ለተባበሩ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል ።
በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች እና ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ እና ጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ ነዋሪዎች ከፍተኛ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በምረቃው አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእውቅናና የሽልማትና ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን በመረሃ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ ፣ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ገመቹ አረቦ፣ የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድአሚን በደዊ እና የክልልና የልዩ ወረዳው አመራሮችና የቀበሌው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ሲል የልዩ ወረዳው መንግስት ኮምኒኬሽን ዘግቧል፡፡
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 