የዶዮ ገና ከተማ መጠጥ ውኃና ሳኒቴሽኝ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ።
መጋቢት 06/2018 ወልቂጤ
በፕሮጀክቱ ግንባታ አፈጻጸምና ቀሪ ስራዎች አስመልክቶ የቢሮው የስራ ሃላፊዎች የፕሮጀክቱ አሰሪ ድርጅት /የUNICEF ዋና መስሪያ ቤት እና የደቡብ ሪጅን ቅርንጫፍ ተወካዮች ፣ እና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የመስክ ምልከታና ውይይት ተካሄዷል ።
በመስክ ምልከታው የተገኙት የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ ከምባታ ዞን የዶዮ ገና መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
የፕሮጀክቱ አብዛኛው የግንባታ ስራዎች በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታና መንገድ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ በጋራ የመስክ ምልከታ ማየታቸውን ገልፀዋል።
ለፕሮጀክቱ የተሳካ ፍፃሜ አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑ ቀሪ የሲቪል ስራዎች፣ የግፊት መስመር ፍተሻና የኤሌክትሮ መካኒካል ሙከራ፣ የመንገድ ከፈታ ፣ የትራንስፎርመር ተከላ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር እስከ መጋቢት 30/2018 ባሉት ጊዜያት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቃ በጊዜ የለኝም መንፈስ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ለዶዮ ገና ከተማ መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አፈፃፀም ከፍተኛውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ለሚገኙ የዩኒሴፍ ፕሮግራም የሥራ ባልደረቦች አቶ ዳዊት በቢሮው ስም አመስግነዋል።
የቢሮ ኃላፊ የመስክ ምልከታውን ተከትሎ በተካሄደው የጋራ ውይይት ቀሪ ተግባራትን ለመፈጸም የጋራ ቅንጅታዊ አሰራርን በመከተል በ24/7 በፍጥነት በቅንጅትና በህብረት ተፈፃሚ እንዲሆን የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ፕሮጀክቱ በጣም ግዙፍና በከፍተኛ ወጪ እየተገነባ ያለ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ የሳኒቴሽን አገልግሎቶችን በትምህርትና በጤና ተቋማት አካቶ የያዘ በመሆኑ በልዩ ትኩረትና ፍጥነት ተጠናቆ ለከተማው ህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ አጽንዖት በመስጠት አንስተዋል።
በመስክ ምልከታው የቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ ጨምሮ የUNICEF ዋና መስሪያ ቤት እና የደቡብ ሪጅን ቅርንጫፍ ተወካዮች ፣ የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮው ምክትልና የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሃላፊ ፣ የከምባታ ዞን አስተዳደሪ አማካሪ ፣ የዶዮ ገና ከተማ ከንቲባ ፣ የዶዮ ገና ወረዳ ዋና አስተዳደሪ፣ የከምባታ ዞን ውሀ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ፣ የቢሮው ዩኒሴፍ ፕሮግራም አስተባባሪ እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 