Skip to main content

ከንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ከውሀ ተቋማት ማስተዳደር ጋር ተያይዞ የተለዩ መልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት አጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ቢሮው አስታወቀ ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳዮችን አፈፃፀምን የሚከታተል ቡድን በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በውሀ ተቋማት አስተዳደር በተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉና የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።

የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደተናገሩት ከመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከህብረተሰቡ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ቢሮው ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመተባበር በእቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ።

በሀይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የውሀ ተቋማትን ከጀነሬተር ወደ ኤሌክትሪክ እና ወደ ሶላር ሲስተም የመቀየር ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል ።

በነባሩ ክልል የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩና የሰነበቱ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በተለይ ነባር ፕሮጀክቶች የስርጭት መስመር ሳይዘረጋ ተዘርግቷል በሚል ለሌብነትና ለብልሹ አሠራር የተደረጉ ፕሮጀክቶችን የህጋዊ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።  

የክልሉ መንግስት ልዩ ድጋፍና ክትትል ታክሎበት በተያዘው በጀት አመት በርካታ ፕሮጀክቶችን መልሶ ወደ ስራ በማስገባት የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል ።

ቢሮው ከንፁህ መጠጥ ውሃ አኳያ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ አቅዶ ከመስራት አንፃር ሰፊ ለውጦችን እያሳየ መሆኑን የገለፁት የክትትል ቡድኑ ሰብሳቢና የክልሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ፈዲላ አደም በከተሞች አካባቢ ያለውን የመጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግና የሚነሱ የውኃ ስርጭት ፍትሃዊነት ጥያቄ ቢሮው ወደ ታች ወርዶ በመስራት ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሄደበት ያለውን ርቀት ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቡድኑ አባል አቶ እያሱ ሻንቆ በበኩላቸው ለመልካም አስተዳደር ችግር መፈጠር ምክንያት የሆኑ አካላት ተጠያቂ ለማድረግ ቢሮው እየሄደበት ያለው ርቀት ሊጠናከር እንደሚገባና በቀጣይ የሕዝብን ክንፍ በማነቃነቅ በቀሪ ጊዜያት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል ።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ የሚከታተል ቡድን በወልቂጤና ሆሳዕና ከተሞች ከንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት አንፃር ያሉ ችግሮችን ለመረዳትና በማመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጥ የተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍሎችን በአካል በማግኘት አነጋግረዋል።

በመድረኩ የቢሮው ምክትል ሀላፊዎች ፣ የቢሮ ኃላፊ አማካሪና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል ።

Image