በሀላባ ዞን ከ187 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን ዌራ እና ዌራ ዲጆ ወረዳዎች ከ187 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
ዛሬ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል በዞኑ ዌራ ዲጆ ወረዳ የሲምቢጣ ቀበሌ መስኖ እና የቁሉቢ ቀበሌ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።
ፕሮጀክቶቹን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ኑርዬ (ዶ/ር)፣ የክልልና የሀላባ ዞን የስራ ኃላፊዎች መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
መሐመድ ኑርዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ክልሉ በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታ ይገኛል።
በክልሉ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በርካታ ቢሆኑም መንግስት ጥያቄዎችን በተቀናጀ መንገድ እየፈታ መሆኑን ተናግረዋል።
የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከፍ ከማድረግ አኳያ ዛሬ የተመረቀው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጠቀሜታው ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።
መስኖ የአየር ንብረት መዛባትን በመከላከል ረገድ ሚናው ጉልህ ነው ያሉት መሐመድ(ዶ/ር)፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማሸነፍ ጠቀሜታው የጎላ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃውንና የመስኖ ፕሮጀክቱን ህብረተሰቡ በባለቤትነት መጠበቅና መንከባከብ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን፣ በዞኑ በተያዘው በጀት አመት የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች ማከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ የመንገድ ችግር መኖሩን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርን ለመፍታት በአበረታች ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉም ብለዋል።
የዌራ ዲጆ ወረዳ በንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውሃ ፕሮጀክቱ ይህን ችግር የሚቀርፍ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ዛሬ ለተመረቁ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከ187 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም አቶ ሙህዲን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር አጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ የሲምቢጣ መስኖ ፕሮጀክት 80 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችልና ከ360 አባ ወራና እማ ወራ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቀሰው፣ ለግንባታው ከ74 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በዘላቂ ልማት ግቦች የሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትልና የቢሮ ኃላፊው ተወካይ ወይዘሮ አሌይካ ሽኩር፣ የቁሉቢ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በአካባቢው ያለውን የውሃ ችግር የሚፈታ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ ለግንባታው ከ73 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 